
ስለ ውቅር አብያተ-ክርስቲያን ሲነሳ ሁላችንም የምናስበው ላሊበላን ነው። ነገር ግን ከአዲስ አበባ ሳንወጣ፣ ከላሊበላ ቀድሞ በ4ኛው ክፍለ ዘመን የተወቀረ ድንቅ ቅርስ እንዳለ ያውቃሉ? በአሁኑ የካ (ከእንግሊዝ ኤምባሲ ጀርባ) የሚገኘው "ዋሻ ሚካኤል"፤ የዮዲት ጉዲትን እሳት የተቋቋመ፣ በጣልያን ቦንብ ጣሪያው የፈረሰ፣ ነገር ግን አሁንም ድረስ የቀደምት ኢትዮጵያውያንን ድንቅ የኪነ-ሕንፃ ጥበብ በኩራት የሚያሳይ ምስጢራዊ ታሪካችን ነው። ሙሉውን ከታች ያንብቡት።
1 min read
ዛሬ ጥቅምት ፬ የኢትዮጵያውያን ወንድማማቾቹ አብርሃ ወ አጽብሃ (ኢዛና እና ሲዛና) የዕረፍታቸው መታሰብያ ነው። የነዚህን ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ ቀን መሰረት በማድረግ ገድለ አብርሃ ወ አጽብሃ ላይ ስለተጠቀሰው በመሃል ሀገር በአዲስ አበባ ስለሚገኝ አንድ ኪነ-ሕንፃ ላውጋችሁ።
የዚህ ኪነ-ሕንፃ ምስረታ እና ታሪክ ወደ 4ተኛ ክፍለ ዘመን ያስጉዘናል። ሁለቱ ወንድማማቾች አብርሃ ወ አጽብሃ በስምምነት እና በአንድነት ሀገር በሚያስተዳድሩበት ግዜ ሰሜኑን አብርሃ ደቡቡን ደሞ አጽብሃ ያስተዳድሩ ነበር። አጽብሃ ታቦተ ሚካኤልን በማምጣት በአዲስ አበባ የካ ከአሁኑ ኢንግሊዝ ኢምባሲ ጀርባ ፍልፍል አብያተ-ክርስቲያን በመስራት አሰፈሩት። ይህንን ቤተ-ክርስቲያን በአሁኑ ሰዓት ዋሻ ሚካኤል በመባል ይጠራል።
ዋሻ ሚካኤል ኪነ-ሕንጻው ከላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያን ጋር መመሳሰል ያለው ሲሆን ነገር ግን ከላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያን ቀድሞ የታነጸ ነው። ዋሻ ሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን ከ20 በላይ ምሰሶ ሲኖረው፤ በስተ ምዕራብ 7 መስኮት፣ በስተ ሰሜን 5 መስኮት፣ እንዲሁም በስሀ ደቡብ 5 መስኮት በአጠቃላይ ወደ 17 ሚገመት መስኮት እንዲሁም በተጨማሪ በስተ ምስራቅና ደቡብ በር እንደ ነበረው ይነገራል።
ይህ ውቅር ቤተ-ክርስቲያን በዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዮዲት ጉዲት ጉዳት የደረሰበት ሲሆን በሁለተኛው የጣልያን ወረራ (1929 - 1933) በቦንብ ጥቃት ሙሉ ለሙሉ ጣርያው ተደርምሷል። በአሁኑ ወቅት ጥቂት ምሰሶዎችና ግርጊዳ የቀሩት ሲሆን አሁን ላይ ከውድመት የተረፈውን ኪነ-ሕንፃ በመመልከት የቀደምት ይዘቱን በአያሌው መረዳት ይቻላል።
ኑ እና የቀደምት የኢትዮጵያውያን ኪነ-ሕንፃ በጋራ እንመልከት!
🗓 መስከረም 27/2016 ዓ/ም
📌 ዋሻ ሚካኤል፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ